በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ማኅበረ ካህናትና ምእመናን በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ማኅበረ ካህናትና ምእመናን በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ

እኛ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የምንገኝ ማኅበረ ካህናት፣ የሰበካ ጉባኤ እና የሰንበት ት/ቤት አባላት ነሐሴ ፳፮ እና ፳፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በፍራንክፈርት ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያ ባደረግነው የሀገረ ስብከታችንን አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በወሰንነው መሠረት፤ ዛሬ መስከረም ፳፮ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም ተገናኝተን ቤተ ክርስቲያናችንና በጥምቀተ ክርስትና ከአብራኳ የተገኙ ምእመናን በአጠቃላይም አገራችን ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ በመመሥረት ሰፊ ውይይት አድርገናል። በውይይታችንም የሚከተሉትን እውነታዎች ተገንዝበናል፦

1. የቤተ ክርስቲያናችን ብሎም የአገራችን ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ የበለጠ እየተወሳሰበ እንደመጣ፣ በዚህ የተነሣም ሕዝባችን ለከፍተኛ የእርስ በርስ እልቂት፣ መፈናቀል፣ ለከፋ ርሃብና እርዛት መዳረጉን፤

2. እንደትናንቱ ኹሉ ለአገር በምትሰጣቸው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ለሕዝብ በመድረስ የምትታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የተለመደ አገልግሎቷን በተሟላ ሁኔታ መስጠት

እንዳትችል፤ ይልቁንም ቤተ ክርስቲያኗንና አማኞቿን አስመልክቶ በቃልም በመጣፍም ሲዘሩ በቆዩ አሉታዊ ትርክቶች የተነሣ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ለከባድ እልቂትና መፈናቀል፣ ቅዱሳት መካናቷም

ለቃጠሎና ለምዝበራ፣ በአጠቃላይ አገራችንና ሕዝቧ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለከፍተኛ ጭንቀትና እንግልት እንደተዳረጉ፤

3. በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮች በዐይነታቸውና በይዘታቸው ዘርፈ ብዙ መኾናቸውን በከባድ ሐዘን ተረድተናል፤

በመኾኑም እኛ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የምንገኝ ማኅበረ ካህናት፣ የሰበካ ጉባኤ እና የሰንበት ት/ቤት አባላት በአጠቃላይ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያናችን ኹኔታ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ለሚከተሉት አካላት ጥሪያችንንም አስተላልፈናል፦

ሀ. ጥሪ ለአገራችን መንግሥት፤

ሕዝብን አስማምቶ በሰላም አኖራለኹ፣ ዜጎች ጉልበት አለኝ ባለ ግለሰብም ይኹን ቡድን ሕይወታቸውን እንዳያጡ፣ ሀብት ንብረታቸው እንዳይማስን ዘብ ኾኜ እቆማለኹ፣ በረሃብ እንዳይገረፉ በበሽታ እንዳያልቁ ልማት አለማለኹ፣ ዜጎችን ለአንድ ዓለማ አስተባብራለኹ በማለት ቃል ገብቶ አገራዊ ሐላፊነትን በመቀበል በትረ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ባለበት አገር እንዲህ ዐይነት ዕልቂትና ውድመት ሲደርስ መታየቱ ምላሽ የማይገኝለት ጥያቄን ይፈጥራል። በመኾኑም መንግሥት ሆደ ሰፊ ኾኖ፤ ምንም እንኳን በርካታ ነፍሳት ካለፉ፣

ሕዝቦችም ከተፈናቀሉና ከተጎሳቀሉ በኋላ ቢኾንም ባለፈው የተከሰተውን አውዳሚ የሰሜኑ ጦርነት በውይይት እንደፈታ ኹሉ አኹንም ነፍሳትን እየቀጠፉ ያሉትንና በኹሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እየተደረጉ ያሉትን ጦርነቶች በውይይት በመፍታት የሀገርን ሰላም፣ የሕዝቧንም አንድነት እንዲመልስ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤

ለ. ጥሪ ለቅዱስ ሲኖዶስና ለመንበረ ፓትርያርክ፤

1. ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ወቅታዊ ችግሮች በሚመከቱባቸውና በሚስተካከሉባቸው መንገዶች ዙሪያ በየጊዜው የሚያቀርቧቸውን ሐሳቦችና ይሁንታዎች ሰምቶና ተቀብሎ የቤተ

ክርስቲያኒቱን መብት እንዲያስከብር፤ በተለይ ቀደም ሲል የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት የሚሳተፉበትን ጠቅላላ የምክክር ጉባኤ እንዲጠራ በድጋሚ እንጠይቃለን፤

2. የቤተ ክርስቲያኗን መልክዕ በመያዝ አደባባይ የሚቆሙ ብፁዐን አበውና አገልጋዮች በአንደበታቸውም ይሁን በአለባበሳቸው የቤተ ክርስቲያኗን ክብርና ማንነት በሚገልጽ መልኩ እንጂ የሌሎችን ዓላማ በሚያስፈጽም መንገድ እንዳይኾን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፤

3. በውጭ ያለችዋ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ ሥራዋን በተጠናከር መልኩ እንዳትሠራ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ በኾነ መልኩ የአንዳንድ ብፁዐን አበው በየአኅጉረ ስብከቱ የሚያደርጉትን ኢ ቀኖናዊ ጉብኝትና አገልግሎት እንዲያስቆም፤

4. መጪዎቹ አጠቃላይ መንፈሳዊና ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤያት የሚከናወኑት የካህናትና ምእመናን በአጠቃላይ የኢትዮጵያውያን ደም እየፈሰሰ ባለበት፤ ተሳታፊዎቹም የምእመናናቸውን ደም

እየተራመዱ በሚመጡበት ሁኔታ በመኾኑ ጉባኤያቱ በወቅታዊው ቤተ ክርስቲያናዊና አገራዊ ቀውስ ላይ ብቻ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኗን ጠንካራ አቋም በመግለጽ ላይ እንዲያተኩር እንጠይቃለን፤

5. ቅዱስ ሲኖዶስ በውጪ ያሉት የቤተ ክርስቲያኗ መዋቅሮች ቢቀናጁና በጋራ ቢሠሩ ለእናት ቤተ ክርስቲያን ደህንነትና አጠቃላይ ጥንካሬ ጠቃሚ በመኾኑ መዋቅሮቹ ጠንካራ የጋራ ግንባር

በሚፈጥሩበት ሁኔታ ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ ቢሰጥ፤

6. በክልል ትግራይ ተቋቋመ ከተባለው መንበር ጋር ተያይዞ በውጪ አገልግሎት ሲሰጡ በቆዩ የክልሉ ካህናት አማካኝነት ቤተ ክርስቲያንን የመክፈል፣ ንብረቷንም የመቀማት እንቅስቃሴ ስለሚታይ

ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን በማእከል ደረጃ የቤተ ክርስቲያንን መብት በሚያስጠብቅ መልኩ አስጠንቶ መመሪያ እንዲያወርድ፤

ሐ. ጥሪ በውጭ ላሉ አህጉረ ስብከት፤

7. በውጭ ያሉ የቤተ ክርስቲያናችን አህጉረ ስብከት በተናጠል የሚሰጡት መዋቅራዊ አገልግሎቶች እንደተጠበቀ ኾኖ እናት ቤተ ክርስቲያን እየደረሰባት ያለውን መገፋት ለመከላከል ጠንካራ የጋራ ግንባር በሚፈጥሩበት ሁኔታ ላይ መክረው ተግባራዊ ቢያደርጉ፤ ያ እስኪኾንም ድረስ የተናበበ ሥራ እንዲሠሩ፤

8. በውጭ ያለችዋን ቤተ ክርስቲያን የሚመሩ መዋቅሮችና አስፈጻሚዎቻቸው የእናት ቤተ ክርስቲያንን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ምእመናን ይገነዘቡ ዘንድ በተጠናና ወጥነት ባለው መንገድ ተከታታይ ገለጻዎች እንዲያደርጉ፤

መ. ጥሪ በኢትዮጵያና በዓለም ላሉ ኦርቶዶክሳውያን፤

9. በመላው ዓለም ያሉ ማኅበረ ካህናት እና ምእመናን ለብሔር ማንነታቸው ሳይኾን ለኦርቶዶክሳዊ ማንነታቸው ቅድሚያ በመስጠት አንድ ኾነው የቤተ ክርስቲያናቸውን እንድነት እንዲጠብቁና እንዲያስጠብቁ፤ ከጥፋት እንዲከላከሉ፤

10.ቤተ ክርስቲያንም አገርም እያለፉበት ያለውን ችግር በአግባቡ ተረድተው እንዲጸልዩ፣ በመካከላቸው ያሉ ልዩነቶችን በውይይት እየፈቱ በእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ዕቅፍ እንዲኖሩ፤ እንዲያጠናክሯትም፤

ሠ. ሀገረ ስብከታችንን በተመለከተ፤

11.ወቅቱ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንና ልጆቿ ብሎም አገራችን ከሀገረ ስብከታችን ማኅበረ ካህናትና ምእመናን ብዙ የሚጠብቁበት በመኾኑ ቤተ ክርስቲያናችን በፈጠረችልን የሀገረ ስብከት መዋቅር የበለጠ ታቅፈን እንድንሠራ፤

12.በወቅታዊው የቤተ ክርስቲያናችንና አገራችን ሁኔታ ላይ የሚመክር የሦስት ቀን ጉባኤ እንድናዘጋጅ፤ ቋሚ ሴሚናሮችንም እንድናዘጋጅ፤

13.ከሌሎች በተለይ በአውሮጳ ካሉ አኅጉረ ስብከት ጋር የበለጠ ተቀናጅተን እንሠራ ዘንድ እስከ አኹን የተደረጉትን እንቅስቃሴዎች አጠናክረን እንድቀጥል፤ ለዚህም እንቅፋት የሚኾኑ ካሉ ቀኖናዊና ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው እንዲኼድ፤

14.በአካባቢያችን ያሉ መንግሥታትና ተቋማት የእናት ቤተ ክርስቲያንንና ኢትዮጵያውያንን ጉዳት ያውቁ ዘንድ ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንድንሠራ፤

15.በማንነታቸውና በእምነታቸው የተነሣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ፤ ዘመዶቻቸውን በግፍ የተነጠቁ ወገኖቻቸው ይጽናኑ ዘንድ በሀገረ ስብከታችን ሥር ያሉ አጥቢያዎች በሚያስተባብሩት

መልኩ እርዳታ እንድናደርስ፤

16.ከዚህ በፊት በተወሰነው መሠረት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በማይቃረን ሁኔታ በሀገረ ስብከቱ ሥር ያሉ አጥቢያዎች መዋቅራዊ አንድነታቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ የተዘጋጀውን ሕገ ደንብ አጥቢያዎች

ተቀብለው ወደተግባር እንዲገቡ እንዲደረግ፤ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር ለአገራችንና ሕዝቦቿ ሰላሙን ይመልስልን።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ማኅበረ ካህናትና ምእመናን

መስከረም ፳፮ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም

ፍራንክፈርት፤ ጀርመን

Scroll to Top