ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ

ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ባሉት ዕለታት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ሥርዓት ኾኖ ይከናወናል፡፡ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ እሑድ ድረስ የሚገኙት ዕለታትም ‹ሰሙነ ፋሲካ› ወይም ‹ትንሣኤ› እየተባሉ ይጠራሉ፤ የየራሳቸው ምሥጢራዊ ስያሜም አላቸው፡፡ ስያሜአቸውንም በአጭሩ በየዕለቱ እግዚአብሔር እንደፈቀደ እንመለከታለን


ከትንሣኤ እሁድ በኋላ ያሉ ዕለታት ስያሜ

ሰኞ (ሰኑይ)
የትንሣኤው ማግሥት ዕለተ ሰኞ „ፀአተ ሲዖል“ ወይም „ማዕዶት“ ትባላለች፡፡ ይኽቺውም ጌታችን በትንሣኤው ነፍሳትን ከሲዖል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ናት! (ዮሐ. 19፥18፤ ሮሜ. 5፥10-17) 

ማዕዶት ማለት መሻገር፣ ማለፍ ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት በፋሲካችን በክርስቶስ ትንሣኤ ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከሃሳር ወደ ክብር መሻገራችንን እናስባለን፡፡


ማክሰኞ
ቶማስ ይባላል፡- በዚህ ዕለት ቶማስ ጌታን አይቶ ማመኑ፤ ጌታዬና አምላኬ ብሎ መመስከሩ ይዘከራል፡፡ ዮሐ. 20፡27-29 

ረቡዕ
አልአዛር ይባላል፡- በዚህ ዕለት ትንሣኤና ሕይወት የሆነው ጌታ ኢየሱስ አልአዛርን ከሞት እንዳስነሳው እናስባለን፡፡ ክርስቶስ የሞትን ስልጣን የሻረ የሕይወት ራስ፤ የመቃብርን ሥርዓት ያጠፋ ትንሣኤ፡ በድልም ያረገ ንጉሥ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡


ሐሙስ
አዳም ሐሙስ ይባላል፡- በዚህ ዕለት ለአዳም የተሰጠው ተስፋ እና የተገባለት ኪዳን እንደተፈጸመ አዳምና ልጆቹ ነጻ እንደወጣን እናስባለን፡፡


ዓርብ
ቅድስት ቤተክርስቲያን ይባላል፡- በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ስለመመስረቷ ይሰበካል፡፡ ክርስቶስ ስለ እርሷ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ቤዛ ሆኖ በደሙ አንጽቶ በትንሣኤው ድል ሰጥቶ እንዳከበራት ይነገራል፡፡ ቤተክርስቲያን ስንል ሕንፃውን ሳይሆን አማኞችን ነው፤ ክርስቶስ ለሕንፃ አልሞተምና፡፡


ቅዳሜ
ቅዱሳት አንስት ይባላል፡- በዚህ ዕለት ቅዱሳት አንስት የክርስቶስን አካል ሽቶ ለመቀባት ጨለማ አቋርጠው ወደ መቃብር መምጣታቸውና ትንሣኤውንም ቀድመው ማየታቸው ይሰበካል፡፡


እሁድ
ዳግም ትንሣኤ ይባላል፡- በዚህ ዕለት ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ ለደቀመዛሙርቱ ተገልጦ ሰላምን መስበኩ እና ሥልጣንን መስጠቱ ይሰበካል፡፡  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሳ በስምንተኛው ቀን በዕለተ እሁድ ደቀ መዛረሙርቱ አይሁድን ፈርተው በተሰበሰቡበት ዝግ ቤቶ „ሰላም ለእናንተ ይሁን „ብሎ ዳግም ስለ ተገለጠ ዳግማይ ትንሳኤ ተብሏል ።


ሁለተኛ ለምን ተገለጠ?


ለሐዋርያው ቶማስ ትንሳኤውን ለማሳመን። የጌታችን ትንሳኤ ቶማስ ስለ ተጠራጠረ ጌታችን ቶማስ በተገኘበት ዝግ ቤት ተገልጦ ለቶማስ ና ወደኔ የተቸነከረውን እጄና ጉኔን ዳስስ ብሎታል። ቶማስም የተቸነከረው እጁን አይቶ የተወጋውን ጉኑ በእጁ ዳስሶ የጌታችን ትንሳኤ አምኗል ።ሃገረ ስብከቱም በሕንድ ስለ ነበረ ተጋድሎውም የፈጸመው እንዲሁም ሰማዕትነት የተቀበለው በሕንድ ነው ።ያቺ የጌታችንን ጎን የነካች (የዳሰሰች)እጅ ሳትበሰብስ ከታቦት ጋር በመንበሩ ላይ ተቀምጣለች ።እስካሁን ድረስ የሕንድ ሊቀ ጳጳስ ሲሾም በዛች እጅ ተመርጦና ተባርኮ እንደሚሾም አንዳንድ ሊቃውንት ይናገራሉ

ሁለተናው ሰንበትን ሊያጸናልን ነው። የአይሁድ ሰንበት፣እግዚአብሔር 22 ፍጥረታትን ፈጥሮ ያረፈባትና እረፉባት ብሎ ያዘዘን ሰንበት ቀዳም(ቅዳሜ)ናት ።በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን የተጸነሰባት ፣ከሙታን መካከል የተነሳባት፣አንዲሁም ደግሞ ለማጽናት ሁለተኛ የተገለጠባት(ዳግማይ ትንሳኤ)፣መንፈስ ቅዱስ የወረደባትና ሐዋርያት ከመጀመርያዋቹ ክርስቲያኖች ጋር በኅብረት ሆነው መንፈሳዊ ስራዋች የሚሰሩባት ቀን ዕለተ እሁድ ነበረች ።ቤተ ክርስቲያናችን ለቅዳሜ ቀዳሚት ሰንበት ለእሁድ ደግሞ ሰንበተ ክርስቲያን እያለች ለሁለቱም ቀናት እኩል ታከብራቸዋለች ።ጌታችንም ይቺ ቀን እረፍትነቷን ለማጽናት ሁለተኛ የተገለጠባት ቀን ናት ።እረፍት ስንልም ስራችንን ትተን ቁጭ ብለን (ተኝተን)የምናሳልፈው ማለት አይደለም ። እንደውም ከማንም ቀን በላይ አብዝተን መንፈሳዊ ስራዎች የምንሰራባቸው ቀናት ናቸው እንጂ።
እንዲሁም ምትሐት አለመሆኑ ለማስረዳት ነወ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምትሐት እንዳልሆነና ቀድሞ የተዋሃደው ስጋና መለኮት ፣ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑ ለማስረዳት ለሁለተኛ ጊዜ ተገልጦላቸዋል ።በዝግ ቤት መግባቱ ደግሞ መለኮት እንዳልተለየውና ስጋ ብቻው እንዳልሆነ ለማስረዳት ነው ። „ብጹዓን እለ እንዘ ኢይሬእዩ የአምኑ“ (ዮሐ20:29)
የተሣተውን ፤ የተረሳው፤ የተገደፈውን፤ የነጠፈውን በቀና መንፈስ አቃንታቹ አንብቡት ስለ ማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን ብርሃነ ትንሣኤውን የገለጸልን አምላካችን ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን!

Leave a Reply

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው