መልአክ የሚለው የግእዝ ቃል ኹለት ትርጉሞች አሉት፡፡ አንደኛው አለቃ፣ ሹም ማለት ነው፡፡ በዮሐንስ ራዕይ ላይ የምናገኛው ሰባቱ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች መላእክት ተብለው መጠራታቸውም ከዚኽ አንጻር ነው /ራዕ. 2 እና 3/፡፡ ኹለተኛውና ከተነሣንበት ርእስ አንጻር ስናየው ደግሞ መልክእተኛ፣ የተሰደደ፣ የተላከ የሚል ትርጕም አለው /ዕብ.1፡14/፡፡ ይኸውም የመላእክት ተግባር ምን እንደኾነ የሚያስረዳ ቃል ነው፡፡ መላእክት ከእግዚአብሔር ወደ ሰው፥ ከሰውም ወደ እግዚአብሔር የሚላላኩ መናፍስት ናቸውና፡፡ መላእክት በሌላ ስማቸው የሰማይ ሠራዊት ተብለው ይጠራሉ፡፡
መላእክት ኹለት ወገን ናቸው:: ብርሃናውያን መላእክትና የጨለማ አበጋዝ የኾነው የዲያብሎስ ሠራዊት የኾኑት እኩያን መላእክት፡፡ ስለዚኽ የእግዚአብሔርን መላእክት ከሌሎቹ መላእክት በአጠራር የምንለያቸው ቅዱስ በሚል ቅጽል ነው፡፡ መላእክት የተፈጠሩት በመዠመሪያው ቀን ነው። ከሰማይና ከምድር ቀጥሎ መላእክት ተፈጠሩ። ኩፋሌ 2፥6-8 ነገረ መላእክት – የመላእክት ተፈጥሮአቸው እመኀበ አልቦ (ከምንም ነው) ነገር ግን ግብራቸውን ለማጠየቅ እንደ እሳት የሚሞቁ እንደ ንፋስ የሚረቁ ስለሆኑ ከነፋስ እና ከሳት ተፈጠሩ ይላል። መዝ 103፥4 መላእክትን ሲፈጥር በነገድ መቶ በአለቃ አስር አድርጎ ፈጥሮአቸዋል። በሶስቱ ሰማያትም ከፋፍሎ አስቀምቶአቸዋል።
መላእክት በፍጥረታቸው ረቂቃን ስለሆኑ ሥጋ እና አጥንት የላቸውም፡፡ አይበሉም አይጠጡም /ሉቃ.24፣39/
መላእክት ጾታ የላቸውም/አያገቡም፡፡ /ማቴ.22፣30 አይዋለዱም አንድ ጊዜ ከተፈጠሩ በኋላ አይጨምሩም አይቀንሱም። ህማም ሞትና ድካም የለባቸውም፤ ሕያዋን ናቸው፡፡ ቁጥራቸው በአኃዝ አይወሰንም /ራዕ.5፣11/
የመላእክት ግብራቸው /ስራቸው:
- እግዚአብሔርን ያለ እረፍት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ ሌትና ቀን ማመስገን ነው፡፡ /ኢሳ.6፣3 ራዕ.4፣8/
- ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ለምህረትና ለብስራታ ለቁጣም ይላካሉ፡፡ /ሉቃ.1፣1-26 ዘፍ.19፣1-38፤ 2 ነገሥ.19፣35…/
- ድኀነት የሚገባቸውን ሰዎች ይጠብቃሉ /መዝ.33፣7 90፣15/ ማቴ.18፣10 የሐ.ሥራ 12፣7/
- ክፉዎችን ይቃወማሉ፡፡ የሐሰትና የዓመጸኛ የክህደት ምንጭና አባት የሆነውን ዲያብሎስን በመጀመሪያ የተቃወሙት መላእክት ናቸው፡፡ /ሄኖክ.12፣3 መቅ.ወንጌል ራእይ. 13፣5 ዮሐ. 8፣44/ /ራዕ.12፣7/
- የቅዱሳንን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያሳረጋሉ፡፡ /ራዕ.8፣2-4 ጦቢ.12፣15/
- ሰውን ያማልደሉ፡፡ ሰው ከፈጣሪው ጋር እንዲታረቅ ይጸልያሉ፡፡ የእግዚአብሔር ባለሟሎች ናቸውና ስለ ሰው ይለምናሉ፡፡
- መላእክት ሰውን ይረዳሉ፡፡ /ዘፍ 16፣7 21፣17፤ 1 ነገሥ.19፣5-7/ ሰውን ይጠብቃሉ፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ጠባቂዎች አሉት፡፡ አንዱ መላእክ ቀን አንዱ ደግሞ ሌሊት ይጠብቁታል፡፡ /ማቴ.18፣10/
- የእግዚአብሔር አገልጋዮችን በችግራቸው ጊዜ ይረዳሉ ያበረታሉ፡፡ /የሐዋ.5፣12-24 12፣1-17 27፣22-25/
- መላእክት ንስሃ በሚገቡ ሰዎች ደስ ይሰኛሉ፡፡ /ሉቃ.15፣10/
መላእክት ይህን የመስላሉ ቁመታቸው ይህን ያህላል ማለት አይቻልም ፡ ረቂቃን ናቸውና ሊያድኑ ያሉትን ለመታደግ በወጣትና በሽማግሌ በተለያዩ አምሳላት ይታያሉ፡፡
ክብራቸውን ስላልጠበቁመላእክት
የመላእክት አለቃ የነበረው ሳጥናኤል ለራሱ ክብርንና አምላክነትን በመፈለጉ በትዕቢቱ ተዋርዶ ሲወድቅ የእርሱ ደጋፊዎችና ተከታዮች የነበሩ መላእክት ሁሉ አብረው ተጣሉ፤ ክብራቸው ተገፎ ከተጣሉ በኋላ ሰይጣን ወይም ዳቢሎስ የሚባል ስም ተሰጣቸው።
በዕብራይሰጥ ሰይጣን ፤ በግሪክ /በፅርዕ/ ዲያቢሎስ ማለት ሲሆን ትርጉሙም ተቃዋሚ ተሰናካይ ማለት ነው። ሰይጣናት ለእግዚአብሔር ስለማይታዘዙ፣ በንስሐም ለመመለስ ስለማይፈቅዱ ለዘለዓለማዊ ፍርድ ወደ ጨለማ ተጥለዋል። ኢሳ 14፥12-15 ይሁዳ 1፥6
ምዕመናንን የመፈታተን የመቃወምና የማሳሳት ስራቸው እንዳለ ነው። መልካቸውን እየለዋወጡ ሰዎችን ሲቃወሙ ይኖራሉ። እዮብ 1፥6 ሉቃ 22፥3 1ኛ ጴጥ 5፥8-9
የመላእክት አሰፋፈራቸው
የመላእክት አሰፋፈራቸው በ ሦስት ሰማያት ሲሆን እነሱም በኢዮር፣ በራማ እና በኤረር ነው።
- በኢዮር፡
ኢዮርን በአራት ከተማ የተከፈለ ሲሆን በእዮር ያሉትን 4 አለቃ 40 ነገድ አድርጎ ከፈላቸው።
ሀ) በኢዮር በላይኛው ከተማ አስሩን ነገድ ስማቸውን አጋእዝት ብሎ በመሰየም አለቃቸውም ይሆን ዘንድ ሳጥናኤልን ሾመው።
ሳጥናኤል ማለት አሀዜ መንጦላኢት/የእግዚአብሔር ታናሽ አገልጋይ ማለት ነው። ወይም ለእግዚአብሔር ቅርብ የሆነ/አቅራቢ ስብሀት ማለት ነው። ኢሳ 14፥9-15
ለ) በኢዮር በሁለተኛው ከተማ አስሩን ነገድ ስማቸውን ኪሩቤል ብሎ ኪሩብ የተባለውን መላእክ አለቃ አድርጎ ሾመላቸው። (ሕዝ 10፥1) እነዚህም የከሀናትና የቀሳውስት አምሳል ናቸው። ተፈጥሮአቸው ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጎ ፈጥሮአቸዋል። እነዚህም ገፀ ሰብ ፣ ገፀ አንበሳ፣ ገፀ ንስር እና ገፀ እንሰሳት ይባላሉ። ከግራቸው ጀምሮ እስከ እራሳቸው ድረስ በአይን የተሸለሙ ናቸው። እንደ ነብር ዥንጉርጉር እንደ መስታውት ብሩህ ናቸው። ሕዝ 1፥2-7 ህዝ 18፥19
ሐ) በእዮር በ3ኛው ከተማ 10ን ነገድ ስማቸውን ሱራፌል ብሎ በመሰየም ሱራፊ የተባለውንም መላእክ አለቃቸው አደረገው። ኢሳ 7፥2 እነዚህም የዲያቆናት አምሳል ናቸው። የምስጋና ምንጭ ከነዛ ይጀምራል ስድስት ስድስት ክንፍ አድርጎ ፈጥሮአቸዋል። ኢሳ 6፥2-4
መ) በእዮር በ4ኛው ከተማ አስሩን ነገድ ስማቸውን ሀያላት (1ኛ ጴጥ 3፥22) በማለት ቅዱስ ሚካኤልን በአለቃነት ሾመላቸው። ሔኖ 10፥2-6 የስላሴ ሰይፈ ጃግሬዎች ናቸው።
- በኢዮር፡
ራማ በተባለው የብርሀን ሰማይ ላይ ያሉትን መላእክት 3 አለቃ 30 ነገድ አድርጎ ከፈላቸው። ራማን ሶስት ከተማ አድርጎ ከፍሏታል።
ሀ) የመጀመሪያዎቹን 10ን ነገድ ስማቸውን አርባብ በማለት ቅዱስ ገብርኤልን አለቃ አድርጎ ሹሞላቸዋል። በመጀመሪያው ከተማም አስቀምጦአቸዋል። ሔኖ 10፥7-8
ለ) በሁለተኛው ከተማ የሰፈሩት አሥሩ ነገድ መናብርት ሲባሉ አለቃቸውም ሩፋኤል ነው። አገልግሎታቸው የመብረቅ ጋሻ፣ የእሳት ጦር ይዘው ዘለአለም እንደንፋስ ሲበሩ ይኖራሉ። ሔኖ 10፥6
ሐ) በራማ በሦስተኛው ከተማ አሥሩን ነገድ ስማቸውን ሥልጣናት (1ጴጥ 3፥22)በማለት አለቃቸው ይሆን ዘንድ ሱርኤል የተባለውን መላእክ ሾሞታል። የስላሴ ነጋሪት መችዎች ናቸው። ለቅዳሴ፣ ለስባሄ ሲያነቁ ሲያተጉ የሚኖሩ ናቸው።
- በኤረር
በኤረር ያለትን/የቀሩትን መላእክት ልክ እንደ ራማ በነገድ 30 በአለቃ 3 አድርጎ አስፈሮአቸዋል።
ሀ) በመጀመሪያው ከተማ 10ን ነገድ መኳንንት (መዝ 3፥24 እስከ 6፥10) በማለት ሰዳክያል የተባለውን መላእክ አለቃ አድርጎላቸው አስፍሮአቸዋል። የስላሴ ቀስተኞች ናቸው። ማቴ 24፥31 ተራራ የሚንድ ድንጋይ የሚሰነጥቅ የእሳት ፍላፃ የእሳት ቀስት ይዘው ሰውን ሁሉ ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስ የሚጠብቁ ናቸው፡፡
በተጨማሪም በትንሣኤ ዘጉባኤ የሰውን ሁሉ አጥንት የሚሰበስቡና ምድርን ለምጽአት እንዲያዘጋጁ የሚላኩ ናቸው፡፡
ለ) በኤረር በሁለተኛው ከተማ አስሩን ነገድ ሊቃናት በማለት አለቃቸው ይሆን ዘንድ ሰላታኤል የተባለውን መላእክ ሾሞታል። የስላሴ የፈረስ ባልደራስ ናቸው። በልባቸው የሚሳቡትን፣ በእግራቸው የሚሽከረከሩትን፣ በክንፋቸው የሚበሩትን የሚጠብቁ መላእክት ናቸው።
ሐ) በኤረር በ3ተኛው ከተማ አሥሩን ነገድ መላክት (1ጴጥ 3፥12) ብሎ ሰይሟቸዋል። አለቃቸውም አናንያ ይባላል። አገልግሎታቸው እንደብረት የፀና የሳት ነጎድጓድን ወደ ምድር የሚወነጭፉ ፀሀይን፣ ጨረቃን፣ ክዋክብትን፣ አዝዕርትን፣ አትክልትን፣ እፅዋትን በላይ በሰማይ በታች በምድር የተፈጠሩትን ሁሉ የሚጠብቁ መላኢክት ናቸው።
እነዚህ መለእክት አርአያቸው/መጠናቸው የተለያየ ነው። ቁመታቸው አምድር እስከ ሰማይ የሚደርሱ መላእክት አሉ። መዝ 84፥3 ዘፍ 38…
በክንፋቸው አንድ ሀገርን የሚያለብሱ መላእክት አሉ። እራሳቸው ተራራ የሚያክል አሉ። መብረቅ ተጎናፅፈው/ለብሰው የሚኖሩ መላእክትም አሉ። በሀሩን ምንጩን በክንፋቸው የሚያቃጥሉ መላኢክት አሉ ማቴ 28፥3 ዮሐ 12፥7


