በዚህ ትምህርት የአምስቱ አዕማደ ምስጢራት ዝርዝር ለምን ምስጢር እንደ ተባሉ ለምን አዕማድ(ምሰሶ) እንደ ተባሉ እንማራለን መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።
አምድ ማለት ምሰሶ ማለት ሲሆን ቤት እንዳይዘም ሚዛኑን እና ልኩን ጠብቆ እንዲቆም የሚያደርግ ነው። አዕማድ ስንልም ምሰሶዎች (ለብዙ )ማለት ነው ። ቤት በአምድ እንደሚጸና ሃይማኖትም በእነዚህ አዕማደ ምሥጢራት መሠረትነት ይፀናልና ነው፡፡
ምሥጢር ስንል በሚታዩ ምሳሌዎች የማይታየውን የሃይማኖት ምሥጢር መረዳት፤ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ ማግኘት ማለት ነው።
ምሥጢር የተባሉበትም ምክንያት
- በሥጋዊ ጥበብ ምርምር መረዳት ስለማይቻሉ::
- ላመኑት እንጂ ላላመኑት ሰዎች የተሰወሩ በመሆኑ ነው፡፡
- በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ ያስገኛልና ነው፡፡
ምሥጢር በሁለት ይከፈላል፡፡ እነርሱም፡-
★የፈጣሪ ምሥጢር ፡- ሊገለጥ የማይችል ነው፡፡ ከ እስከ የሌለው ምሥጢርም ይባላል፡፡
★የፍጡራን ምሥጢር ፡- በጊዜ ሂደት የሚገለጥ (የሚታወቅ) ነው፡፡ የሰውና የመላእክት
አምስቱ አእማደ ምሥጢር የሚባሉት፡-
- ምሥጢረ ሥላሴ፦የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የምንማርበት
- ምሥጢረ ሥጋዌ፡ የአምላክን ሰው መሆን የምንማርበት
- ምሥጢረ ጥምቀት፡ ስለ ዳግም መወለድ የምንማርበት
- ምሥጢረ ቁርባን፡ ስለ ክርስቶስ ሥጋና ደም የምንማርበት
- ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን፡ ስለ ዳግም ምጽዓት የምንማርበት ነው፡፡
- ምሥጢረሥላሴ
ሥላሴ ሥንል ልዩ ሶስትነት ልዩ አንድነት ማለት ነው፡፡ የሥላሴ ሦስትነት በአካል ፣በስምና በግብር ነው፡፡
★ የስም ሦስትነት፡ አብ ፣ወልድ፣መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ፡፡አንዳቸው በሌላው ስም አይጠሩም፡፡ይህ ስማቸው ግን ግብራቸውን የሚገልጥ ነው፡፡ ለአብ ፍጹም ስም አለው አብ ተብሎ ይጠራል እንጂ በወልድ ወይም በመንፈስ ቅዱስ ስም አይጥራም። ለውልድም ለመንፈስ ቅዱስም እንዲሁ ፍጹም ስም አላችው። ይህም ስማቸው በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጠቅሰዋል። ‹‹ አህዛብን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዝሙራቴአድርጓቸው››ማቴ28፤19
★ የግብር ሦስትነት በግብር አብ ወላዲና አስራጺ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስም ሠራጺ/ከአብ የወጣ/ነው፡፡
★ የአካል ሦስትነት፦ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ፍጹም አካል፣ፍጹም ገጽ፣ፍጹም መልክ አላቸው ማለት፡፡ ይህ አካል ዝርው (ብትን) ያልሆነ ረቂቅ መንፈሳዊ አካል ነው፡፡
★አብ ወልድን ወለደ ስንል ከአካሉ ከባሕርይው ፤ አስገኘው ማለት ነው፡፡
★ወልድ ከአብ ተወለደ ስንል አብን አክሎ አብን መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው፡፡
★አብ መንፈስ ቅዱስን አሰረጸው ማለት ፤ ከአካሉ ከባሕርይው አስገኘው ማለት ነው፡፡
★መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሰረጸ ስንል አብን አህሎ አብን መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው፡፡
የሚከተሉትን ጥቅሶች ስንመለከት የሥላሴን አንድነትና ሶስትነት ያሳያሉ፡፡
ዘፍ 1፥26 እግዚአብሔርም አለ፦ስውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር።
እግዚአብሔርም አለ ብሎ አንድነቱን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር ሲል ደግሞ
ብዛትን ( ሦስትነት ) ይገልጻል።
ዘፍ 3፥22 እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ። ከእኛ የሚለውና እንደ አንዱ የሚለው እግዚአብሔር ከአንድ በላይ እንደሆነ የጠቆመን ናቸው።
ዘፍ 11፥7 ኑ፥ እንውርድ አንዱ የአንዱን እንዳይስማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው። ኑ የሚለው ቃል የሚያስርዳን አንዱ አካል ሌሎችን ሁለትና ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል መጥራቱን ነው።
ዘፍ 18፥1-15 በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ አድባር ዛፍ ተገለጠለት። ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ስዎች በፊቱ ቆመው አየባቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተንሥቶ እሮጠ ፥ወደ ምድርም ስገደ፥እንድህም አለ፥በፍትህስ ሞገስን አግንቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ።
ኢሳ 6፥1-3 ቅዱስ፥ቅዱስ፥ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኸ ነበር። አንዱ ቅዱስ ለአብ ሁለተኛው ቅዱስ ለወልድ ሦስተኛው ቅዱስ ለመንፈስቅዱስ መሆኑን ልብ እንበል። ይህንን በድጋሜ ራዕይ 4፥8እናገኘዋለን።
ኢሳ 48፥16… አሁንም ጌታ እግዚአብሔር እና መንፈሱ ልከውኛል።
ማቴ 3፥16 ኢየሱስም ከተቀመጠ በኃላ ወድያው ከውሃው ወጣ፤እነሆም፤ስማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱም ላይ ሲመጣ አየ፤ እነሆም፥ድምጽ ከስማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።
ማቴ 28፥19 እንግድህ ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ በወልድን በመንፈስቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዝሙር አድርጓቸው፤እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድርስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።
ሉቃ 1፥35 መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑል ኃይል ይጽልልሻል ስለዚህ ደግሞ የሚወለደው የእግዚአብሔር ቅዱስ ልጅ ይባላል።
ዮሐ 14 ፥ 25 ከእናንተ ዘንድ ሲኖር ይህን ነግሬአቹኃለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከውን ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔ የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።
1ኛ ቆሮ 12፥3 ስለዝህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር። ኢየሱስ የተርገመ ነው የሚል እንደሌለ ፥ በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር። ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል እንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ።
2ኛ ቆሮ 13፥14 የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ የእግዚአብሔር ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ህብርት ከሁላችሁ ጋር ይሁን።
የሥላሴ አንድነት
በመለኮት፣በአገዛዝ፣በሥልጣን፣ይህንን ዓለም ፈጥሮ በማሳለፍ ፣በፈቃድ እና በመሳሰሉት ነገሮች አንድ ናቸው፡፡
# በህልውና አንድ ናቸው ማለት አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው/ይኖራል/፣ ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ውስጥ ህልው ነው፣ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ውስጥ ህልው ነው፡ዮሐ14፤8-11
# በመለኮት አንድ ናቸው ስንል በመፍጠር፣በመስጠት፣በመንሳት፣በማዳን፣በመግደል፣በ ማጽደቅ፣በመኮነን ይህንን በመሳሰሉ ሁሉ አንድ ናቸው ማለት ነው፡፡
#ሥላሴ እግዚአብሐር በመባል አንድ ናቸው፡፡ ዘዳ 6፤4 2ኛቆሮ13፤14; የሐዋ20፤28; ሐዋ5፤3-6;
የሥላሴን # አንድነትና # ሶስትነትበምሳሌ
- የሰውነፍስ
ኩነት ወይም ከዊን ማለት ሁኔታ ወይም መሆን ማለት ሲሆን ፣ ይህም በሰው ነፍስ ምሳሌ ይገለጻል ። ነፍስ አንዲት ስትሆን ሶስት ባህርያት (ኩነታት ) አሏት ፤ እነሱም ፤ ልብ (ማሰብ ) ፤ ቃል (መናገር ) ፤ እስትንፋስ (ሕይወት ) ናቸው ። ከሶስቱ ባህር ያት አንዱ ከተጓደለ ነፍስ የሚለውን ስም ልታገኝ አትችልም ። ይኸውም አብ በልብ (ማሰብ ) ፣ ወልድ በቃል (መናገር ) ፣ መን ፈስ ቅዱስ በእስትፋስ (ሕይወት ) ሲሆን አብ ለራሱ ልብ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው ። ወልድም ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው ። መንፈስ ቅዱስም ለራሱ ሕይወት ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው ። በእግዚአብሔርነቱ ፤ ልብ ፣ ቃል፣ ሕይወት አለ ። ነፍስ ሶስት ባህርያት ቢኖሯትም አንድ እንደምትባል እግዚአብሔርም በስም፣ በአካል፣ በግብር ሶስት ቢባል አንድ አምላክ እንጅ ሶስት አማልክት አይባልም ። ዘዳ 6 ፥4 ፡ ሚል 2፥10::
- ፀሀይ
ክበብ ብርሃን ሙቀት አላት ። በክበቧ አብ ፣በብርሃኗ ወልድ ፣ በሙቀቷ መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆነው ቀርበዋል ። ፀሀይ ሶስት ሁኔታዎች ሲኖሯት አንድ እንደሆነች እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ።
- ውሃ
ይዘት፣ እርጥበት ፣ ቅዝቃዜ አለው ። በይዘቱ አብ ፣ በእርጥበቱ ወልድ ፣ በቅዝቃዜው መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ ። ውሃ አንድ እንደሆነ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ። ሌሎቹም በምሳሌነትየሚቀርቡ ፍጥረታት አሉ ። ነገር ግን ሁሉም በምሳሌነታቸው
ለማስተማር እንጅ የአምላክን : ባህርይ # የፍጡር ባህርይ ሊያስረዳ አይችልም ።
- ምሥጢረሥጋዌ
ማለት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆን ነገር ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት፡፡ እነዚህም፦ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ ያለው ልደት፦ ይህ ልደት ዘመን አይቆጠርለትም፡፡ በዚህ ልደት ምክኒያት ከአብ እና መንፈስ ቅዱስ ጋራ መቀዳደም የሚባል ነገር የለበትም፡፡ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ለዓይን ጥቅሻ ያህል እንኳ ምንም መቀዳደም የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁለተኛው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ
በመንፈስ ቅዱስ ግብር መወለዱ ነው፦ በዚህ ጊዜ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በምድር ላይ ሕሙማነ ነፍስን በትምህርቱ ሕሙማነ ሥጋን በተአምራቱ ፈውሷል፡፡ ዘመን ተቆጥሮለታል፡፡ ሰው የመሆኑም ነገር በተዋሕዶ ነው፡፡ ሥጋ የሥጋ ባሕሪን ሳይለቅ መለኮት የመለኮትነት ባሕሪን ሳይለቅ ማለት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፍፁም ሰው ፈፁም አምላክ ብለን ነው የምናመልከው፡፡ አስቀድሞ በነቢያት ትንቢትና በመልአኩ ብሥራት እንደተነገረ ቅድስት ድንግል ማርያም
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወለደችው፡ ስሙንም አማኑኤል አለችው፡:
አማኑኤል ማለት እግዚአ ብሔር ከእኛ ጋራ ነው ማለት ነው። ኢሳ 7.14፡ ማቴ 1.22-24፡ እርሱም ስሙ! ድንቅ፡ መካር፡ ኃያል አምላክ፡ የዘለዓለም አባት፡ የሰላም አለቃ፡ ነው ኢሳ 9.6-7፡፡ ስለዚህም እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ (አምላክን የወለደች) ናት፡፡ በመዉለዷም ድንግልናዋ አልተለወጠምና ዘለዓለማዊት ድንግል ናት፡ ሕዝ 44.1-3፡ ሉቃ 1.35-39።
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ።” ዮሐ.1፥1፡: ይህ መጀመሪያ፡ መጀመሪያ የሌለው መጀመሪያ ነው። ይህ መጀመሪያ ዘፍጥረት 1:1 ላይ ከተጠቀሰው መጀመሪያ ከተባለው ይለያል፡፡ ቃል የተባለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያ የሌለው መጀመሪያ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነበረ ነውና። ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር ሳይቆጥር የባሪያን መልክ ይዞ፤ ባርነትን ሰብሮ ልጅነትን የሰጠን ነው እንጅ። ዮሐ.1:2: ፊልጵ. 2:7፣ ዮሐ.1:14:: የማይታየው አካላዊ ቃል በሚታይ ሥጋ ተገለጠ። ጸጋና እውነትም በእርሱ መገለጥ ተገለጡ፡፡ የማይዳሰሰው በሚዳሰስ ሥጋ ተዳሠሠ። ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ተቆጠረለት። ሥጋን የተቆራኘውን የሞት ሥልጣን በሞት ለመሻር የማይሞት ባሕርይ ያለው
ቃል የሚሞት ሥጋን ነሳ። ዕብ.2:14-18:: ለዘመኑ ጥንት ለኑሮው ፍጻሜ የሌለው የሰው የዘር ሀረግ ውስጥ ገባ። ማቴ.1:1-14 ዮሐ1፥14።
አምላክ እንዴት ሰው ሆነ? ቢሉ በተዋሕዶ ያለመለወጥ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመደመር።
አምላክ ለምን ሰው ሆነ? ያሉ እንደሆነ
– ለቤዛነት ፦ ቤዛ ማለት ምትክ፣ ካሳ፣ ጥላ ማለት ነው፡፡ በእኛ ላይ የወደቀውን የሕግ ርግማን ለመሻር፤ ምትካችን ሆኖ ሞታችንን ሊሞትልን ሰው ሆነ።
– ለአራያነት፡- ሰው ሊኖረው የሚገባው ትክክለኛ አኗኗር በክርስቶስ ኑሮ ተገልጿል፡ ትሕትና፡ ይቅርታ፡ ፍቅር፡ ትዕግስት፡ ሰላማዊነት……
- ምሥጢረጥምቀት
ጥምቀት ማለት በውሃ መነከር መላ አካላትን በቅዱስ ውሃ መዘፈቅ ማለት ነው፡፡ የጥምቀት መስራች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የተጠመቀው በዘመነ ሉቃስ ማግሰኞ ጥር 11 ቀን ሌሊት በ30 ዘመኑ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ነበር፡፡ሉቃ. 3፥23/ በዚህ ጊዜ ሰማይ ተከፈተ ማቴ 3፥17፡፡ ማለትም ምሥጢር ተገለጠ፡፡ ምሥጢረ ሥላሴ አብ በደመና ሆኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ሲል፥ ወልድ በተለዬ አካሉ በባሕረ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ፥ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ጌታችን ተጠምቆ ሲወጣ በእርግብ
አምሳል ሲወርድ ታዬ ተሰማ፡፡ ምሥጢረ ሥላሴ ገሃድ ሆነ፡፡
ጌታችን ጥምቀቱን ለምን በዮርዳኖስ አደረገው? ቢሉ፡
- ትንቢትን ይፈፅም ዘንድ፡፡ ‹‹ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ›› /መዝ.113፥3/
- ሕዝብና አሕዛብን አንድ ለማድረግ ዮርዳኖስ ከላይ አንድ ሆኖ ዝቅ ብሎ ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡
- እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምደረ ርስት ገብተዋል፡፡ ያመኑ የተጠመቁ ምዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡
- ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ ባርነታችንን የሚገልፀውን ደብዳቤ በዮርዳኖስ ጥሎ የነበረውን ይደመስስልን ዘንድ /ቈላ. 2፥14/
ጌታችን ለምን በሌሊት ተጠመቀ? ቢሉ
- ጌታችን እፀድቅ አይል ፃድቅ ነው፤ እቀደስ አይል ቅዱስ ነው፥ ስለምን ነው ቢሉ፤ በኃጢአት ጨለማ ስለነበረ ሕዝብ የጽድቅ ብርሃን እንዲወጣለትና ብርሃን የሆነ ወንጌል መገለጡን ለማሳየት ነው፡፡ ኢሳ. 9፥2
- አንድም ጌታ ልደቱ፣ ጥምቀቱ፣ ትንሣኤው እንዲሁም ምጽአቱ በሌሊት ነው፡፡ ይኽም የሆነበት ምክንያት ሌሊቱን ተከትሎ የሚመጣው ብርሃን በመሆኑ ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት የመሸጋገራችን ምሳሌ ነው፡፡
- አንድም መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል የሚወርድ ነውና በጌታ ላይ የወረደው ርግብ እንጂ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ባሉ ነበር፡፡ በሌሊት ርግብ የለም ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ፡፡
መንፈስ ቅዱስ ለምን ጌታ ከውኃ ከወጣ በኋላ ወረደ? ቢሉ
- ዮሐንስን ያከብሩት ነበርና መንፈስ ቅዱስ የወረደው ለዮሐንስ እንጂ ለጌታ አይደለም ይሉ ነበርና ምክንያቱን ጌታ ውኃ ውስጥ እያለ ከዮሐንስ አልተለየም ነበርና፡፡
- ውኃን የሚባርክ መልአክ እንዳለ ያውቁ ነበርና ውኃውን ለመባረክ አንጂ ለጌታ አይደለም እንዳይባል፡፡
- ማረፊያ ያጣች ርግብ በባሕር ስትበር አረፈችበት ባሉ ነበርና ሐሳባቸውን በሙሉ ያጠፋ ዘንድ ከውኃ ውስጥ ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወረደ፡፡
ጌታችን መጥተህ አጥምቀኝ ማለት ሲችል ወደ ዮሐንስ ሄዶ የተጠመቀው ለምንድን ነው? ቢሉ
- ጌታችን የመጣው ለትህትና ስለሆነ
- አንድም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለመደንገግ ነው፡፡ ማለትም ጌታችን ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ብሎት ቢሆን ኖሮ በዚህ ዓለም ያሉ ነገስታትና ወዛዝርት የቤተክርስቲያን አባቶችን (ካህናትን) ቤታችን ድረስ መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ወደ ቤተክርስቲያን ሂዶ ይጠመቅና ያስጠምቅ ዘንድ ይህን አደረገ፡፡
ዮሐንስ ጌታን ሲያጠምቀው እጁን ሳይጭንበት በአርብቦ ነው፤ ለምን አልጫነበትም? ቢሉ
- እጁን ጭኖበት ቢሆን ኖሮ ዮሐንስ በጥምቀት አከበረው /ልዕልና ሰጠው/ የሚሉ መናፍቃን ይነሱ ነበርና፤ ይህን ለማጥፋት፡፡
- ገለባ እሳት ውስጥ ቢገባ ይነዳል ወደ አመድነትም ይቀየራል፡፡ ገለባ የተባለ የሰው ሥጋ እሳተ መለኮትን በእጅ መንካት አይችልምና፡፡
ጌታችን ዝቅ ብሎ 28, 29-ከፍ ብሎ 31, 32-ሳይሆን ለምን በ30 ዘመኑ ተጠመቀ? ያሉ እንደሆነ፡፡ ይህም ምክኒያት አለው፡፡
- የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በዕድሜና በዕውቀት የበሰሉ፣ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው ወደ መሆን የሚደርሱት በዚህ የእድሜ ወሰን ነውና /ዘፀ. 4፥3፤1ዜና መዋ. 23፥24፤ 1ጢሞ. 3፥6-10/ ያንን ሥርዓት ለማጠየቅ ነው፡፡
- ዮሐንስ መጥምቅም የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ይሁዳ ምድረ በዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30 ዓመት ዕድሜው በኋላ ነበር፡፡
- አንድም የሰው ሁሉመጀመሪያ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40ኛ ቀኑ ተሰጥቶት ኋላም በኃጢአት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፡፡
የጌታችን ጥምቀት ከምእመናን ጥምቀት በምንይልያል? ቢሉከላይ እንዳየነው እርሱ እፀድቅ አይል ፃድቅ ነው፡ እቀደስ አይል ቅዱስ ነው፡፡ ነገር ግን በነብያት የተነገረውን ትንቢትን ፈፅሞ የእኛን ልጅነት ይመልስ ዘንድ ነው፡፡ የእኛ ምዕመናን ጥምቀት ግን ለድህነት ነው፡፡ በዮሐ ወንጌል ምዕ.3፥3 እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በስተቀር መንግስተ ሰማያትን አያይም፥ አይወርስም እንዲል፡፡
- ምሥጢረቁርባን
ቁርባን በቁሙ ስጦታ (አምሃ) ማለት ሲሆን ስለ አማናዊው ስጦታ ስለ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የምንማርበት (የምናውቅበትና የምናሳውቅበት) የትምህርት አምድ ነው፡፡
★የምሥጢረ ቁርባን መሥራች ማን ነው?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስቅለቱ ዋዜማ በዕለተ ሐሙስ ምሥጢረ ቁርባንን ሕብስቱን ባርኮ ቀድሶ ወይኑን ባርኮ ቀድሶ ወደ አማናዊ ሥጋውና ደሙ በመለወጥ መሠረታት፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን ራሱ ቆርቦ ቀጥሎ ቅዱሳን ሐዋርያትን ምግብን ከበሉ ከጠጡ በሗላ አቁርቧቸዋል፡፡ ሕብስቱና መጠጡ የተዘጋጀውም ከሥንዴና ከወይን ነበር፡፡ „ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንስቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፥ ጽዋንም አንስቶ አመስግኖ ሰጣቸው፥ እንዲህም አለ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው“ ማቴ 26፥27-
ይህም አማናዊ ሥጋውና ደሙ ነው፡፡
„እውነት እውነት እላችሗለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፥ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ፥ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው“ ዮሐ 6፥51-60::
ሕብስቱንም አንስቶ ጽዋዉንም አንስቶ ወደ ሰማይ አየ ምንዲን ነው ካሉ፤
- ይህ ሕብስት ጽዋ ሥጋዬ ደሜ መሆኑ ፍቃዴ እንደሆነ ፍቃድህ ይሁን ሲል ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በፍቃድ አንድ ናቸውና ዮሐ 10፥30::
- ሕብስቱንና ወይኑን አንስቶ መባረኩ፦ ከሕብስት ወደ አማናዊ ሥጋው መለኮት ከወይን ወደ አማናዊ ደሙ ለመለወጥ ነው፡፡
ስለምን ጌታችን ራሱ ቆርቦ ቀጥሎ ሐዋርያትን አቆረበ ቢባል፥ አርአያ ይሆነን ዘንድ ነው፡፡ እርሱ መጀመሪያ ሳይቆርብ አቁርቦ ቢሆን ኑሮ ካህናት እኛ አንቆርብም ይሉ ነበርና፡፡ ቆርባችሁ አቁርቡ ሲል ነው፡፡
እኛ ምእመናን ቁርባን የምንቀበለው በባዶ ሆዳችን በፆም ነው፥ ሐዋርያትን ግን ያቆረባቸው ከበሉ ከጠጡ በሗላ ነው፡፡ ይህ ምንድን ነው ቢሉ። መስዋዕተ ኦሪት በምግብና በመጠጥ ይደረግ ነበር፡፡ መስዋዕተ ወንጌል ታላቅ መሥዋዕተ ኦሪት ታናሽ መሆናቸውን ለማጠየቅ ነው፡፡
ጌታችን ምሥጢረ ቁርባንን ለምን በሚበላና በሚጠጣ አደረገው? በሌላ ነገር ለምን አላደረገውም የተባለ እንደሆነ፡
★በመብል በመጠጥ የመጣውን ኃጢአት በመብል በመጠጥ ለማጥፋት ሲል
★መብል መጠጥ ከሰውነት ጋር ይዋሐዳል፥ ስለዚህ ከሰውነታችሁ ጋር ይዋሐድ ሲል
★መብል መጠጥ ያፋቅራል፥ ስለዚህ ሥጋውና ደሙ ያፋቅራል ሲል…ነው፡፡
ጌታችን ቁርባንን ሕብስቱን በስንዴ፣ መጠጡን በወይን ለምን አደረገው ቢባል፡
★ምሳሌውን አማናዊ ለማድረግ ነው መዝ 4፥7
★ጌታችን ስንዴ ይመገብ ነበርና አማናዊ ሥጋዬን ሰጠሗችሁ ሲል ነው
★ስንዴ ስብ ሥጋን ይመስላል፥ በመሠለ ነገር ለመስጠት ሲል
★ስንዴ ባለሙያ ቢይዘው ንፁህ ነው፥ ስለዚህ ነውር ነቀፋ የሌለበት ሕግ ሰራሁላችሁ ሲል
★በልጅነቱ ወይን ይጠጣ ነበርና አማናዊ ደሜን ሰጠሗችሁ ሲል
★ወይን መልኩ ቀይ ነው፥ ቀመሰለ ነገር ሰጠሗችሁ ሲል
★ወይን በተተከለ በ3 ዓመቱ ያፈራል፥ 3 ዓመት አሥተምሬ ደሜን አፈሰስኩላችሁ ሲል
★ወይን ግንዱ ደካማ ሆኖ መንገድ ቢያሳዩት፣ ቢንከባከቡትና ቢደግፉት አምሮ ለምልሞ መልካም ጣዕም ያለው ፍሬን ያፈራል፥ የጌታችንም ደም በሃይማኖት ለፀና በምግባር ለቀና ቢሰጡት መልካም ፍሬ ያፈራልና ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በክርስቶስ የተመሰረተች ናትና ሥጋውን ያልበላ ደሙንም ያልጠጣ ሕይወት የለውም እያለች ዘወትር ታስተምራለች፡፡ በሃይማኖትና በምግባር ታንፀው ለሚመጡም ልጆቿ ዘር፣ ቀለምና ፆታ ሳትለይ ለሁሉም ታድላለች፡፡
- ምሥጢረትንሳኤምውታን
ትንሳኤ የሚለው ትርጉም መነሳት፣ በሞት ተለያይተው የነበሩ ነፍስና ሥጋ ዳግም መገናኘትና መነሳት ነው፡፡
ሰው ሲፈጠር ነፍስና ሥጋው ሳይለያዩ ለዘለዓለም እንዲኖር ነበር፤ ነገር ግን ሕገ እግዚአብሔርን ሲያፈርስ ሞት በሰው ልጆች ላይ ነገሰ፡፡
ፈፅሞ በስብሰን እንቀር ዘንድ የማይፈልገው እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ተወልዶ ተሰቅሎ ሞቶ የትንሳኤያችን በኩር ሆኖ ተነስቷል፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ሞት ድል የተነሳበት የሰው ልጅ ነፃነት የታወጀበት ነው፡፡ የትንሣኤ በኩር ማለትም ሞትን በኃይሉ ድል ያደረገውና ለሚያምኑበት ይህን ሥልጣን የሰጠው ጌታችን ክርስቶስ ነው፡፡ „ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩር ሆኖ ከሙታን ተነስቷል“ 1ኛ ቆሮ 15፡2ዐ፡፡ ጌታችንም ሞትን ድል አድርጎ 3 ቀን 3 ሌሊት በከርሰ መቃብር አድሮ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል እንደተናገረው በራሱ ኃይልና ሥልጣን ተነስቷል፡፡ የእኛንም ትንሳኤ በእርሱ ትንሳኤ ቀድሶታል፡፡ ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞትም ይነሳል ዮሐ 5፥26 በማለት፡፡
የሙታን አነሳስ „ሙታን የማይፈርሱ ሆነው ይነሳሉ፥ ይህ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን፣ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ይለብስ ዘንድ አለው“ 1ቆሮ 15፥52-54:: ስለሆነም በመጨረሻው ጊዜ ሰው ሁሉ (ጻድቃንም ኃጥአንም) ማለትም ወንድ የ30 ዓመት እንዲሁም ሴት የ15 ዓመት ሆነው ይነሳሉ፡፡አነሳሳቸው ግን ይለያያል፡፡ መልካም የሰሩ እንደ ፀሐይ አብርተው ተውበው አሸብርቀው የክብር ትንሳኤ ሲነሱ፥ ክፉ የሰሩ ደግሞ ፅልመት ለብሰው ከሰል መሥለው የሃሳር ትንሳኤ ይነሳሉ፡፡ „በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፥ መልካም ያደረገ ለሕይወት ትንሳኤ ክፉም ያደረገ ለክፉ ትንሳኤ ይወጣሉና“ ዮሐ 5፥28:: በግብራቸውም ፃድቃን በበግ፥ ኃጥአን ደግሞ በፍየል ተመስለዋል፡፡ ፃድቃን የአባቴ ብሩካን ተብለው በቀኝ ሲቆሙ፥ ኃጥአን ደግሞ እናንተ ርጉማን ተብለው በግራ ይቆማሉ፡፡


